Daniel 10

ዳንኤል በራእይ ያየው ሰው

1የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ብልጣሶር ለተባለው ዳንኤል ራእይ ታየው። መልእክቱ እውነት ነው፤ ስለ ታላቅ ጦርነትም የሚገልጽ ነበረ
ወይም እውነትና ከባድ ሸክም ነበር
። መልእክቱንም ይገነዘብ ዘንድ በራእይ ማስተዋል ተሰጠው።

2በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ለሦስት ሳምንት አለቀስሁ፤ 3ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ምርጥ ምግብ አልበላሁም፤ ሥጋም ሆነ የወይን ጠጅ ወደ አፌ አልገባም፤ ቅባትም አልተቀባሁም።

4በመጀመሪያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ፣ 5ቀና ብዬ ስመለከት፣ በፊቴ በፍታ የለበሰና በወገቡም ላይ ምርጥ የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ። 6አካሉ እንደ ዕንቍ፣ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዐይኖቹ እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደ ጋለ ናስ የሚያብረቀርቁ፣ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር።

7ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሀት ስለ ወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ። 8ስለዚህ ይህን ታላቅ ራእይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጕልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኀይልም አጣሁ። 9ከዚያም የቃሉን ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ፣ በግንባሬ በምድር ላይ ተደፍቼ በከባድ እንቅልፍ ተዋጥሁ።

10እነሆም፣ አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤ እየተንቀጠቀጥሁም በእጄና በጕልበቴ አቆመኝ፤ 11እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ወዳንተ ተልኬአለሁና፣ የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ። ይህን ሲለኝም፣ እየተንቀጠቀጥሁ ተነሥቼ ቆምሁ።

12ደግሞም እንዲህ አለኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አትፍራ፣ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንህበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ። 13ነገር ግን የፋርስ መንግሥት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያ ከፋርስ ንጉሥ ጋር ተውሁት። 14ራእዩ ሊፈጸም ገና ብዙ ዘመን ስለሚቀረው፣ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚሆነውን ልገልጽልህ አሁን ወደ አንተ መጥቻለሁ።”

15ይህን እየተናገረኝ ሳለ፣ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፤ የምናገረውንም ዐጣሁ። 16ከዚያም የሰው ልጅ የሚመስል
አብዛኛዎቹ ማሶሬቲክ የጥንት ቅጆች እንዲሁ ሲሆኑ፣ ከማሶሬቴክ አንድ የጥንት ቅጅ፣ የሙት ባሕር ጥቅልሎችና ሰብዓ ሊቃናት ግን ከዚያም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ይላሉ።
ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እኔም አፌን ከፈትሁ፤ መናገርም ጀመርሁ፤ በፊቴ የነበረውንም እንዲህ አልሁት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ከራእዩ የተነሣ ተሠቃይቻለሁ፤ ኀይልም ዐጣሁ።
17ጌታዬ ሆይ፤ ጕልበቴ ከዳኝ፤ መተንፈስም አቅቶኛል፤ እኔ አገልጋይህ ከአንተ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ?”

18እንደ ገናም፣ ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም። 19እርሱም፣ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና” አለኝ።

እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበርትተኸኛልና ተናገር” አልሁት።

20እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ለምን ወደ አንተ እንደ መጣሁ ታውቃለህ? የፋርስን አለቃ ለመውጋት በቶሎ እመለሳለሁ፤ እኔም ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21አስቀድሜ ግን በእውነት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ ከእነዚህ አለቆች ጋር ለመዋጋት ከአለቃችሁ ከሚካኤል በስተቀር የሚረዳኝ የለም።”

Copyright information for AmhNASV